የሶሻል ሚዲያው ግብግብ: ኢትዮጵያን እናፈርሳለን የሚሉትን ዛሬ ዝም ብሎ ማየት እንደማገዝ ይቆጠራል!

 

ሶሻል ሚዲያ ለአገር ወዳዶችም ሆነ ኢትዮጵያን እናፈርሳለን ለሚሉ ጅሎች ዛሬ የእኩል ጨዋታ ሜዳ ነው።ይህ ጽሁፍ የሶሻል ሚዲያን ጠንቅ እና ጥቅሙንም በጣም ባጭሩ ለመዳሰስ እና ምን ይደረግ ብሎ ለመጠይቅ የቀረበ ጽሁፍ ነው።ለአገር አጥፊም ሆነ በጎ ነገር ሊደረግበት የሚችል ሚሊዮኖች ሰፍረው የሚውሉበት የሚያድሩበትም የህብረተሰባዊ መገናኛ መድረክ ነው።መልክቱ አገር ወዳዶች የውነት ሰራዊት ሆነን መነሳታችን ዛሬ የግድ ነው።ኢትዮጵያን እንወዳታለን እያልን ቆመን ስትፈርስ እንዳናይ ልንሰጋ ጠንክረንም ልንሰራ ይገባናል!

አሁን ብቅርቡ ኔት ፍሊክስ በተሰኘው የፊልም ተቋም ሶሻል ዲሌማ (Social Dilemma) “ህብረተሰባዊ አስቸጋሪ ሁኔታ” የተሰኘውን ዘጋቢ ፊልም (documentary) ለቋል።ፍሬ ነገሩ ሶሻል ሚዲያ ህብረተሰብ ላይ ምን አደረሰ? ጠቀመ ወይስ ጎዳ? ምን ያልታሰበ ነገር ፈጠረ? ወደፊቱስ እንዴት ይሆናል? የሚል ነው።ዓለምን ጉዳዩ እንዲህ ሲያሳስብ እኛ ኢትዮጵያውያንን ደግሞ ይህ ዓለምን እግዚኦ የሚያሰኝ ነገር ውድ አገራችንን ምን ያደርጋት ይሆን ብለን የሚያሳስበን መሆኑ አልቀረም።በአገራችን አባቶች ቀድመው ነገሩን ለይተውታል።”ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” ይከፋል ብለው ተናግረዋል።ለሾል ሚዲያ እንዴት የሚመች አነጋገር ነው።በፊልሙ የቀረቡት በስራ መስኩ የረቀቀ ችሎታ ያላቸው ስለሆኑ የነገሩን አስፈሪነት ያጎላዋል።ሆኖም በእምሯችን የሚንቃጨለው በሶሾል ሚዲያ ምክንያት ጥንታዊት ኢትዮጵያ ልትደፈር? የሚል ስጋት ነው።ልቡ ያበጠበት ውርጋጥ ሁሉ ተነስቶ አፈርስሻለሁ የሚላትን አገር ሰው እያለ እንዴት ለጉዳት ትዳረግ ብለን ልንቆጭ አይገባም?ሶሻል ሚዲያ ዋዛ አይደለም።ብዙ የከፉ ገጥታዎች አሉት።

ዛሬ ሃብታም ደሀ አገር ሳይል ይህ ዘመን ያመጣው የመገኛና መድረክ በዓለም ላይ ተንሳራፍቷል።ከምንዳስሰው፤ለምንኖርበት ዓለም ሌላ ዓለም ተፈጥሮልን በዚያ ዓለም ውስጥ ቀኑን እንውላለን፤እናድራለንም።እንዱ ያለም ክፍል ሲያሸልብ ሌላው ከእንቅልፉ ተነስቶ ይቀጥላል።እንቅልፍ ሲያሸልበን ብቻ ከዚያ ሜዳ እንወጣለን።ሱስም ያሲዛል።መለየት የሚቻል አይደለም።የሚቆጣጠረን አባዜ ነው።አቅደው መድረኩን የሚያሾሩት ዛሬ በመንግስት ላይ መንግስት ናቸው።ከብረዋል።መንግስት ቢሻቸው መፈንቀል ይችላሉ!አንድ ሰው ሊወደድ ሊጣላ ሊወገዝ አምሮውንም እንዲስት እራሱንም እንዲያጠፋ ሁሉ በቢጤዎቹ የአምሮ ጭንቀት እንዲያስገድደው ሊሆን ይችላል።ሶሻል ሚዲያ ላይ ውሸት ባፍ ከሚውራው እጅግ በጣም ፈጥኖ ይጓዛል።ውሸት ሲደጋገም እውነት ይመስላል ይባላል።ሶሻል ሚዲያ ለድግግሞሹ ምቹ ነው።እውነትና ውሸቱ ይደባለቃል።ፍትህ ይዛባል!ጥበበኞቹ ሲተቹት ዓለምን ያዛባል ያጠፋል እስከማለትም የሚሄዱ አሉ።

በሶሻል ሚዲያ መንግስትም የሰውን ነጻነት ሊገፍበት ይቻለዋል።መንግስት ሶሻል ሚዲያን መዝጋት ይችላል።ሲደረግ አይተናል።ህወሃት ለ30 ዓማታት ያደርገው አይደል? ሌላ ምሳሌ ሰሞኑን ዩጋንዳ “ምርጫ” ሲደረግ በፕሬዚዳንቱ ትዛዝ ፌስ ቡክ ተዘግቷል።ሰሜን ኮርያ እና ቻይና ሶሻል ሚዲያን አጥረውታል።ኢራን ግብጽም ጨቋኝ ሁሉ ለፕሮፓጋንዳው ይጠቀምበታል።አደገኛ ነው። ሜይናማር በሚባለው የእስያ አገር ንጹሃን ሰዎች በሃይማኖት እምነታቸው ተለይተው እንዲጨፈጨፉ ካገራቸው እንዲሰደዱ መሆኑን ዓለም ታዝቧል።የዓለም ትልቁ ዴሞክራሲ የህንድ አገርም በፌስ ቡክ በሚስተባበር የመንጋ ፍርድ የእስልምና ተከታዮች ተገድለዋል፤ተውግረዋል።ተሸማቀው እንዲኖሩ ተደርገዋል።አድራጊዎቹ የሚደራጁት በፌስቡክ ነው። ”በለው!” “እዚያ ጋ ናቸው!” የሚባለው ቅንብር በፌስ ቡክ ነው።ቅን የሚያስቡ ደግሞ ብዙ መልካም ነገሮች ብፌስ ቡክ ያከናውናሉ።በአረቡ ዓለም አምባ ገነኖችን ፍግል ፍግል ያደረገ ሶሻል ሚዲያ አልነበረም?

ቅን ላሰበ በሶሻል ሚዲያ ፍቱን የትግል መሳሪያም ነው። ከላይ የቀረበው መንደርደሪያ ሜዳውን እንድንቃኘው የዚህን መሳሪያ ከባድነትም አደገኛነትንም እንድናስበው የተሰነዘረ ሃሳብ ነው።አሁን ወደ ኢትዮጵያችን ጉዳይ እንዡር።

በህወሓት ድቀት ከሁለት ወራት በፊት በክፋት ሃይሎች ጅማሮ ጦርነት ተከፍቶ በመከላከያ እና በታጠቁ የህወሓት ሃይሎች መካከል የነበረውን ውጊያ ወጎን አድርገን ለየት ያለውን ብናይ በማይካድራ ባንድ ጊዜ አንድ ሺህ ንጽሃን በአሰቃቂ ሁኔታ ተጨፍጭፈዋል።ባገራችን ያልተለመደ በመሆኑ ደነገጥን፤አዘንን።ብሽቀት እና ምሬት የመጣው ግን ማን እዳደረገው እኛ እያወቅን የዓለም ሚዲያ ድርጊቱን የሁለት ወገን ሲያደርገው፤የዘር ጥላቻ ብሎ ሲፈርጀው ፖላቲካውን ከውስጡ መጦ የጎሳ ግጭት አድርጎ ሲያወርደው ነው።”ትግሬና እማራ አይዋደድም” “የዘር ጉዳይ” ነው በማለት ውሸት ሲነዛበት እና ህወሓቶች አሰቃቂው ድረጊት ፈጻሚ መከላከያ እና የአማራ ክልል ሚሊሻ እንደሆነ ሁሉ አድርገው ሲያቀርቡት ነው።እኛ ብናውቅም ለባእዳኑ ህብረተሰብ እውነታው ተዛብቶ ቀረበ።በተለይ ደግሞ የህወሓት ቅጥረኞች የሆኑ ባእዳን ሶሻል ሚዲያ ላይ ሲያቀላጥፉት የከፋውን ድርጊት አዛብተው አቅርበው ይሄው አሁንም አለ።ይህ የሆነው የሶሻል ሚዲያ መንገዱ ስለሚመች ነው።ሶሻል ሚዲያ ለጥ ያለ ሜዳ በመሆኑ አፍና ብእር ያላቸው ሽምጥ ይጋልቡበታል።የማይ ካድራ ግፍ እንደ ኢትዮጵያዊ፤እንዳ አፍሪካዊም ሲያስቡት ያበግናል!ያስመርራል!አገር ወዳዶች እጅግ ብዛት ኖሮን ተደራጅተን ድምጽ ብናሰማ ይህ ባልሆነ ነበር!ይቆጫል።

ሲጀመር እኮ ማንም ቴክኖሎጂን ለክፋት መስሪያ አላሰበውም።ለኮምፑተር እድገት ፋና ወጊ ከሆኑት ከጀመሩት ሰዎች እነ ስቲቭን ጆብስ ኮምፑተርን ለሰው ኧምሮ ስራ ረዳት ብለው ነው ያሰቡት።አእምሮን የሚያፍታታ የሚሻሽል ማለት ነው።ደጉን ብናስበው እውቀት ተስፋፍቷል፤እውቀትን መጋራት ቀላል ነው።አንድ ሰው የፈቀደውን ሲማር ሊውል ይችላል።ያልታሰበው ውጤት ግን ያስፈራል።ለምሳሌ ማይካራን መካድ!የማይካራን ወንጀል ማላከክ ከሚያስፈራው ይመደባል።ይዘገንናል!ሶሻል ሚዲያ ላይ ጉልበት ያለው ይሰማል።ብዙ ሰራዊት ያለው ለጊዜውም ቢሆን ይረታል፤ድምጹ ያይላል!።እውነቱ እስከሚወጣ የሚጠብቅ እና ትግስትም ጊዜም ያለው የለም።ዓለም ትሮጣለች!ማንም ስልክ እና ኮምፑተር ያለው ግው ብሎ የሚሰፍርበት ፌስቡክ አለ።እውቀት ስልጣን ሙያዊ ትስ ስር ያለው ደግሞ ትዊተር ከሚባለው መለስተኛ ሜዳ ይገኛል።ትዊተር 330 ሚሊዮን ሰዎች አሉት።ዓለምን የሚዘውረው የሰው ዘር እዚያ ትዊተር ላይ አለ።አደጋው እስቲ እንየው፦

ሶሻል ሚዲያ የእኩል ቤት ይመስላል።ግን አይደለም! ምሳሌ ትዊተር በሚባለው መድረክ የተመዘገበ ሁሉ ሃሳቡን ይሰጣል።የወደደውን አዎን ይላል።የጠላውን ያጣጥላል።ይራገማል! የተቆጣ ይሳደባል! ስልጣን ያለው፤ጋዜጠኛው ሊቁ ጠበቃው ከያኒው ታሪክ አዋቂው ሁሉም የሚሰለፍበት ነው ትዊተር።አብዛኛው ስነስራትን ጨዋነትን ተከታይ ነው፤ለውነት በውነት የሚከራከር ነው።ስለስራት ተገቢ ነው።ታዲያ ውሸታምም አለ።የኧምሮ ችሎታውን ለቅጥር ስራ ያቀረበ ቀበኛም አለ።ከፈረንጅም ካገር ዜጋም ቅጥረኛ አለ።ከእንግሊዞች ፈረንሳዮች ኖርዊጂያኖች ኢትዮጵያን ስራዬ ብለው ሲያዋክቡ የሚውሉ አሉ። ክፋቱ እንዲህ ነው። እኒህ ቅጥረኞች ከጋዜጠኝነት እና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተቆራኙ ናቸው።መንግስታት ደግሞ ይሰሟቸዋል።በስራቸው አይቦዝኑም።ምሳሌ የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ ያለውን እርዳታ አልሰጥም ሲል እኒህኑ ቅጥረኞችን ሰምቶ ነው።ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ ተባብረን ብንናገር ኖሮ እንዲህ ባልሆነ ነበር።በትዊተር ግን ኦነግና ህወሃቶች ለጉትን ፈረንጆቹ ቅጥረኞች ግብ ያስገቡታል።የኢትዮጵያ አገራችንን መከራ ያበዙታል።በዳይ ክፉ አድርገው ያቀርቧታል።ታዲያ ዝም ማለታችን እንዴት አስወቃሽ አይሆንም?

ልብ ማለት የሚገባው ህወሓት እና አጋዦችዋ ብቻ አይደሉም ሶሻል ሚዲያን ለክፋት የሚያውሉ ሌሎችም አሉ።በኢትዮጵያ ጉዳይ ብሄርተኛው ኦነግም ሌላ ስራ የለውም።የንጹሃን ሞት በወለጋ፤ቤንሻንጉል፤በሸዋ በየትም ቢሆን የመጤ ሞት ስለሆነ ዝም ነው።ሶሻል ሚዲያ ላይ ሌላ ነገር ተይዞ ወይም ከታሪክ ተጣሞ ሲነዛ ይውላል።ለፈረንጅ እና ለግብጽ ሲያሳብቅ ይውላል! በፈጠራም እነኦነግ ሸኔን ያጀገናሉ።አገር ፈረሰ ይላሉ።ሌላ ደግሞ ፈረንጅ በቁንጽል ከያዛት የህብረተሰባችን እውቀቱ ተነስቶ አዋቂ ተብሎ “ኤክስፐርት” ተብሎ የሚነዛው እንቶ ፈንቶ አደንቋሪነት በድምጻቸው ያጅባሉ።የተቀናበረ ነው።ሾሳል ሚዲያን ለትግል አለማዋል ኋላ ቀርነት ነው።አላዋቂነትንም ጨምሮ!

ሾሳል ሚዲያ በዘመነ ኮቪድ ቅልጥ ያለ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጊያ ሜዳ ነው።ሰብሰብ ደርጀት ያሉ፤ዝግጅት ያደረጉ የሚመለከተውን ሁሉ እየጠቀሱ ድምጻቸውን ያሰሙበታል።እንደ ህወሃት ጀሌዎች ያሉ ደግሞ አልሞትንም ይሉበታል።ዛሬ መአት ያወሩበታል።ዝም ከተባሉ ሌላው ከሜዳ ይወጣል ማለት ነው።እንዲሁ አገሬን ወዳለሁ ምን ያደርጋል?ያልመከተ ይፈነከታል!

የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለፉት አርባ አመታት ነው ዓለምን እንዲህ አድርጎ የቀየረው።ኢትዮጵያ በህወሓት ጭቆና ለሰላሳ ዓመታት ተቀፍድዳ የዚህ ቴክኖሎጂ በጣም ትንሽ ጠብታ ነው የደሰረሳት ማለት ያስችላል።እንዲያውም በግምት ለውጡ ከመጣ በሁዋላ የሆነው ይልቅ ከ1991 እስከ 2018 ከሆነው እድገት ይበልጣል የሚያስብል ነው።ጉዳዩ ጥናት የሚሻ ነው።የህወሃት አፈና የአገር እድገትን አፍኖት ኖርዋል።ኢትዮ ቴሌኮምን ህወሓቶች አያስነኩም ነበር።ከኢትዮጵያ ይልቅ ዛሬ ኬንያ እና ዩጋንዳ በቴክኖሎጂ ይልቃሉ።

ህወሓት ሶሻል ሚዲያን እንደፈራችው ኖራ አሁን አልፋለች።በጽሁፍ የነደፋቸውን ጋዜጠኛ ያስሩ ያሰቃዮ ያሰድዱ ነበር።ሶሻል ሚዲያ አይያዝ አይጨበጥ።ሲባዛባቸው ድርግም ያደርጉት ነበር እንጂ እስተ መጨረሻው ችግራቸው ነበር።የእነሱ እድገት ማምጣት የስለላ ቴክኖሎጂ ማስገባት ነበር።በፖለቲካ ህወሓት ከገጠሙት መካከል ፌስቡክን በተለይ በስራ ያዋሉት የነገሱበትም እነጅዋር መሃመድ ነበሩ።ኋላ ግን ልክ እንደ ህወሓት የስልጣን ነገር ላይ በባዶ ሙዝዝ ብለው ችኩል ጅብ ሆነው ወደቁ እንጂ።አሁን እየደመደምን እንሂድ።

ዛሬ የዓለም ፖለቲካ በትዊተር ላይ ሲከካ ሲቦካ ይውላል ቢባል ስተት አይሆንም።የዓለም ፖለቲካ ዘዋሪዎች ወይ በዝምታ ሲአያስተውሉ ወይም ሲሳተፉ ይውላሉ።አንድ የአገር መሪ ወይም ባገር ያለ የፖለቲካ ተቃዋሚ መሪ ሃሳቡን፤ተቅውሞውን ልክ እንደማንም ሊያሰማ ይችላል።መንግስት ለመንግስትም ሲዋረፍ ይውላል።አንዳንዱ ደግሞ እንደ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ያለው መረን ለቆ ህዝብ ለህዝብ አነሳሳህ ተብሎ ከናካቴው የሚወገድም አለ።

በሾሻል ሚዲያ ተገናኝቶ፤ተቧድኖ ለበጎ ተግባር ምሰለፍ ይቻላል።በአንጻሩ ግን መንግስት መገልበጥ ሙከራ የዳዳቸውም አሉ።እነጃዋርን እናስታውስ።ተጨማሪ ምሳሌ የፕሬዚዳንት ትራምፕ ደጋፊዎች የአሜሪካ ምክርቤት ሂደው ህግ አውጭዎችን ለመግደል መሰለፋቸውን ዓለም ተከታትሎታል።ታዲያ ያው ህግና ስራት ያቸንፋልና አሁን ሁሉም ተለቅመዋል።የሚገርመው በሶሻል ሚዲያ የሚጠነጠነው የሴራ ፖለቲካ ወይም የሴራ ንድፍ (እንዲህ ሊሆን ነው conspiracy) ልብ አንጠልጥል ውሸት ነው።ለመሆኑ ለትራምፕ ደጋፊዎች ምንድንነው በሶሻል ሚዲያ የተነገረው? ለትራምፕ ዳጋፊዎች የተሰበከው “በመንግስት ውስጥ የሰይጣን አማኞች ተከታዮች አሉ።በመንግስት ውስጥ ሆነው ፕሬዚዳንት ትራምፕን የሚቃወሙ፤ ልጆችን የሚያጠቁ ሰው ባላዎች ናቸው።ትራምፕ በቀን በቀን እንዚህን ይታገላል ነው።”ውሸቱ ተነግሮ ተቀባይ አግኝቷል።አገር ቀውጢ ሆንዋል!ስጋት ፈጥሮ መንግስት ዛሬ በ20 ሺህ ጦር ዋሽንግቶን ዲ ሲን ዛሬ ይጠብቃል።የአዲሱ የባይድን በዓለ ሲመት ይረበሻል ተብሎ በመስጋት ትልቅ ሽብር አለ።

የሚያቀናብሩት ያውቁበታል።ቀምመው አዘጋጅተው ይለቁታል ተከታዩ እውነት/ውሸት ተግ ብሎ ሳይመዝን ተቀብሎ ያሳልፈዋል። ይዛመታል።ሶሻል ሚዲያ እንዲህ ነው።ድሮ በልጅነታችን የምናውቀው ጋዜጠኝነት ዛሬ ጎድፏል።እውነት መናገር ሳይሆን ላይክ እና ሰብስክራይብ መሰብሰብ ሞቅ ደመቅ ማድረግ ተመራጭ ሆንዋል።ጋዜጠኛ የተባለው ብዙ ለከፈልው የሚሰራ ሊሆን ይችላል።በሶሻል ሚዲያ ውሸት እውነትን ሲጥ ታደርጋለች።የአገራችን ሁኔታ እንዲህ አሳሳቢ ሆኖ አያውቅም።

ይህን ሁሉ ያሰኘን የአገራችን የኢትዮጵያ ጉዳይ አሳሳቢነት ነው።አገር በቋፍ ስትሆን ቀጣይ ጥቃት የሚደርስባት በዚሁ በገለጽነው ሶሻል ሚዲያ ሲሆን እያወቅን ዝም ካልን እኛም ከአፍራሾቹ ጋር ሳናውቀው ተዘናግተን እያፈረስን ነው ማለት ነው።ዝም ምርጫ አይደለም!ቀድሞ የጮሀ ይሰማል ውሸታምም እንኳን ቢሆን እድል አለው!ሶሻል ሚዲያ ግድ አይሰጠውምና።

2021 ወሳኝ ዓመት ነው።አገር ወዳዶች መበርታት አለብን! ኢትዮጵያ አገራችን የምታደርገው ሽግግር መልክ ይዞ ተረጋግታ ልናይበት እንችላለን።ካልተጋን ደግሞ እኒህ የዘረዘርናቸው ሃይሎች ድል ይቀናቸውና ያገራችን ጉዳይ አስጊ ሁኔታ ላይ ይወድቃል ማለት ነው።ጉዳዩ የዚህን ያህል ግልጽ ነው።እያንዳንዱ አገሬን እወዳታለሁ የሚል ካልተጋ ኋላ ጠጠቱ የሚቻል አይደለም።ሊያርሙት የሚቻልም ስተት አይደለም።በትግራይ ጉዳይ፤በቤንሻንጉል፤በወለጋ፤በሱዳን ጠረፍ በግድቡ በምርጫው የሶሻል ሚዲያ ተኩስ በየጎራው ነው።እሩቅ ያለችው ሩሲያ የአሜሪካን አገርን ምርጫ ጉድ ሰርታዋለች።አጠገባችን ያለችው ጠላት ግብጽ የምታስበው ለአንባቢ መተው ነው።የሱዳንንም ትንኮሳ ጨምረን። አገር እናድን!ካንድ ጥፋት ዳነች ሲባል ሌላ ደግሞ ተተክቷል።የትግራይም መረጋጋት ብዙ ልፋት ጠያቂ ነው።

በዳያስፖራ ላለን ኢትዮጵያን የምናድንበት አንድ እድል ነው ያለን።በፌስቡክ፤በትዊተር፤ በቴሎግራም ባሉት መንገዶች ሁሉ ለመታገል እንነሳ! በአገራችን በጀግንነት የሚዋደቁትን ከውጭ ያለን ተገን እንሁናቸው።

ኢትዮጵያ አገራችን ለዘለዓላም ትኑር! 

በ ጋሻው ገብሬ

Share via
Copy link
Powered by Social Snap